የዮሐንስ ወንጌል ክፍል 12 | ታላቅ መገለጥ | በወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን | THE GOSPLE OF JOHN | By Evangelist Yared Tilahun
"ታላቅ መገለጥ" የሚል ስያሜ የሰጠሁት የዮሐንስ ወንጌል ክፍል 12 በውስጡ የታመቁ በርካታ እውነቶች አሉ። ነጥቦቹን እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ። “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።” ዮሐ. 1፥18 1. ለምን አልታየም? ሀ. ባሕሪው ስለሆነ! 5፥37፣ 6፥46፣ ሮሜ 1፥20፣ 1ጢሞ. 1፥17፣6፥16 1ዮሐ. 4፥12፣ ዕብ. 11፥27፣ ቆላ. 1፥15 ለ. ሰው አይቶት ሊድን ስለማይችል ዘጸ. 33፥20 ሐ. የሚታየው በልጁ 12፥45፣ በሥራው ሮሜ 1፥20፣ በእርስ በርሳችን ፍቅር 1ዮሐ. 4፥12 2. አንድስ ስንኳ አላየውም ሲል ስለ ማን መናገር ፈልጎ ነው? ስለ ሙሴና እግዚአብሄርን ለማየት ስላቀረበው ጥያቄ። ዘጸ. 33፥20 3. በአባቱ እቅፍ ያለ (ኮልፖስ) በማዕድ ላይ ከጎን የሚቀመጥ፣ ወደ ደረት የሚጠጋ፣ ከዚህ በላይ ሊቀርብ እስከማይችል ድረስ የቀረበ። ዮሐ. 13፥23 4. አንድ ልጁ (ሞኖጌኔስ) አንድያ፣ አንድ እና ብቸኛ፣ ልዩ። ዮሐ. 3፥16፣ የሞተው የመበለቲቱ ልጅ ሉቃስ 7፥12፣ የመቶ አለቃው ሴት ልጅ ሉቃስ 8፥42፣ ጋኔን ይጥለው የነበረው ልጅ አባት ሉቃስ 9፥38። ዕብ. 11፥17 ልዩ ልጅ (እስማኤል ነበርና)፤ 1፥12 ብዙ ልጆች ተወልደዋል፣ የእሱ ልጅነት ግን ልዩ ነው። አንዳንድ የእንግሊዘኛ ትርጉሞች “እርሱ ራሱ እግዚአብሔር የሆነ አንድ ልጁ” ይላሉ። 5. እርሱ ተረከው፦ አየው ብቻ ሳይሆን ተረከው። ማቴ. 11፥27 በመጀመሪያ በአባቱ ፈቃድ መላውን ፍጥረት ካለ መኖር ወደ መኖር በማምጣት ገልጦታል (1፥2)፤ በዘመናት ውስጥ በነቢያት አፍና በቅዱሳት መጻሕፍት በመናገር ገልጦታል፣ አሁን ደግሞ በሥጋ በመምጣት ገለጠው። ይህ የመገለጦች ሁሉ አውራ እና ቁንጮ ነው። ተግብሮት፦ 1. እግዚአብሄርን ማወቅ በራሱ መታዘዝ ነው። “እወቁ!” ተብለናልና። የምናመልከው፣የምንኖርለትና የምናገለግለው ባወቅነው መጠን ነው። 2. ሊታይ የማይቻለውን በኢየሱስ ክርስቶስ (በወንጌል) በኩል ለማየት ቻልን። 2ቆሮ 4፥6 ምን ያህል አይተናል? 3. ጌታ ኢየሱስ አብን ይህን ያህል በቃሉና በሥራው ከገለጠው፣ እኛስ ኢየሱስ ክርስቶስን ምን ያህል በኑሯችንና በሥራችን እየገለጥነው ነው?